“ስምምነቱ የአወልያን የትምህርት አገልግሎት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋገር ነው” ― ሀጅ ሰኢድ አስማረ
የካቲት 17፣ 2017 ዓ.ል | ሻዕባን 25 ፣ 1446 ዓ.ሒ
بِسْمِ ٱللَّهِ ٱلرَّحْمَٰنِ ٱلرَّحِيمِ
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
“ስምምነቱ የአወልያን የትምህርት አገልግሎት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋገር ነው” ― ሀጅ ሰኢድ አስማረ
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
አዲስ አበባ |
አወልያ የእርዳታና ልማት ድርጅት የትምህርት ስርአቱን አካታች ለማድረግ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትበትን ስምምነት ከአብደላህ ኢብኑ ኡሚ መክቱም የቁርአን ማህበር ጋር ተፈራርሟል።
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ስር የሚተዳደረው አወልያ እርዳታና ልማት ድርጅት ከተመሰረተበት ዕለት ጀምሮ ለዜጎች የትምህርት፣ የጤና እና መሰል አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።
የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ሀጅ ሰኢድ አስማረ በፊርማ ስነ ስርአቱ ላይ እንደገለፁት ከተመሰረተ 72 ዓመታትን ያስቆጠረው አወልያ አገልግሎቱን ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት እና ባህል ሳይለይ እየሰጠ ይገኛል።
ሀጅ ሰኢድ አክለውም ድርጅቱ በየወቅቱ ያጋጠሙትን ፈተናዎች በፅናት በመቋቋም በትምህርቱ ዘርፍ ከእራሳቸው አልፈው ለሀገርና ለህዝብ የተረፉ ዜጎችን ማፍራት ችሏልም ነው ያሉት።
የትምህርት ጥራትንና የማህበራዊ ዘርፍ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት በርካታ ስራዎችን እየሰራ የሚገኘው አወልያ የትምህርት ስርአቱን አካታች ለማድረግ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትበትን ስምምነት ከአብደላህ ኢብኑ ኡሚ መክቱም የቁርአን ማህበር ጋር ተፈራርሟል ብለዋል።
የአብደላህ ኢብኑ ኡሚ መክቱም የቁርአን ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ከድር መህሙድ በበኩላቸው ስምምነቱ ዐይነ ስውራን ሀይማኖታዊ ማንነታቸውን ጠብቀው እንዲማሩና ለትልቅ ደረጃ ደርሰው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የአወልያ እርዳታና ልማት ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል ፈንታው በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት በርካታ መስዋዕትነት የተከፈለለት አወልያ ለዚህ ታላቅ የማህበራዊ አገልግሎት መድረሱ ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ አባላት እድል መሆኑን ገልፀው ዛሬ የተጀመረው የአካቶ ትምህርት የበለጠ እንዲሰፋ አመራሩ በትኩረት ይሰራል።
በስምምነቱ መሰረት አወልያ እርዳታና ልማት ድርጅት ከ2018 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ከአብዱላህ ኢብኑ ኡሚ መክቱም የቁርአን ማህበር የሚቀበላቸውን 20 ዐይነ ስውራን ተማሪዎች ከሌሎች ጋር አካቶ የሚያስተምር ይሆናል።
አወሊያ ቴሌግራም
http://t.me/awoliaschool5
