ለ17 ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የአወልያ ሆስፒታል ህንጻ እና ሌሎች የተቋሙ ግንባታዎች ተጠናቀው ተመረቁ።

አንጋፋውን የእስላማዊ የልማት ተቋም አወሊያን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ከ17 ዓመት በላይ በጅምር ቆሞ የነበረው የሆስፒታል ህንፃ ግንባታ በመጠናቀቁ ትናንት ሚያዚያ 09/2014 ታላላቅ ኡለሞች፣ ዱኣቶች፣ ባለሀብቶች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል። የህንፃው ግንባታ ያለቀ ቢሆንም ሆስፒታሉን አግልግሎት ለማስጀመር የ4 ወር ጊዜ ሰሌዳ እንደተያዘለት እና በቀጣይ ስራ የህንፃውን አሳንሱር (ሊፍት) መግጠም እና የህክምና መሰሪያዎችን ማሟላት እንደሚጠበቅ ታውቋል።በተመሳሳይ ሁኔታ የአንዳኛ ደረጃ ት/ቤት አዲስ ባለ 4 ክፍል አንድ ብሎክ የተመረቀ ሲሆን፣ እድሳት የተደረገላቸው የጀናዛ ማጠቢያ እና የመሰብሰቢያ አዳራሽም መጠናቀቃቸውና ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን የአወሊያ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ጀማል ሙሀመድ በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር ይፋ አድርጓል።የቦርዱ ሰብሳቢ አክለውም ሲገልፁ ከላይ የተገለፁት የልማት ስራዎች የተሰሩት አምና በተደረገው “አወሊያን የማዳን ጥሪ” ዘመቻ ከኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የተገኘ 17 ሚሊዮን ብር መሆኑን ጠቅሰው ይህ አበረታች ውጤት ቢሆንም ተቋሙ ካለው ታሪክ፣ ለሙስሊሙ ከሚሰጠው ጥቅም፣ እና ከህዝበ ሙስሊሙ ቁጥር አንፃር አነስተኛ መሆኑን በቁጭት ተናግረዋል። ድርጅቱ አሁንም ቢሆን ለደመወዝ ክፍያ እና አስተዳደራዊ ወጭዎች በአሰቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ እና ሁሉም ሙስሊም ከተቋሙ ጎን እንዲቆም የጠየቁት የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ሃጅ ሰኢድ አስማረ በበኩላቸው በቀጣይም ተቋሙን ለማሸጋገር የሚያስፈልጉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ጠቁመው የህዝበ ሙስሊሙ “የአይን ብሌን” እና ታሪካዊ ተቋምን ለማልማት በተግባር ትኩረት ሰጥቶ ህዝቡ እንዲረባረብ አደራ ብሏል። እንደሚታወቀው አወሊያ በመጅሊሱ ስር ከሚተዳደሩ የልማት ተቋማት አንዱ ቢሆንም ከሰኔ 2012 ዓል ጀምሮ የመጅሊሱ ፕሬዝደንት በየወሩ 1.3 ሚሊዮን ብር በጀት ድጎማ በማቆም “ከፈለጋችሁ ዝጉት” በማለታቸው ተቋሙ ሙሉ በሙሉ የመዘጋት አደጋ ተጋርጦበት ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *